Updates
ስላም ወገኖች
ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ የአዲስ ተስፋ ወንድሞች ህብረት መመስረት እውን መሆንን እያበሰርን ይህን ግብረሰናይ ማህበር ለማቋቋም አነሳስቶ ለፍፃሜም እንዲበቃ የረዳንን የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ የሆነውን አምላክችንን እያመሰገንን ይህንንም ዓላማ ከግብ ለማድረስ በቅን መንፈስ በመነሳሳት ከፍተኛ ትብብር በማድረግ ዋጋ ለከፈሉት የህብረቱ መስራች አባላትም እጅግ የከበረ ምስጋና ይድረሳቸው እንላለን።
የአዲስ ተስፋ ወንድሞች ህብረት ዓላማና ግብ በመረዳት የራዕዩና የተልዕኮው ደጋፊና ተባባሪ ለመሆን ለምትፈልጉ ወገኖች ሁሉ የህብረቱን ድህረገፅ በመጎብኘት አስፈላጊውን ዝርዝር መረጃ ማግኘት የምትችሉ መሆኑን በደስታ እንገልፃለን።
የዚህ ህብረት ዋና ዓላማ ከዘር; ከሃይማኖትና ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ በሆነ መንገድ በሰብአዊነት ብቻ ላይ በመመስረት ቤተሰብን; ማህበረሰብንና ሃገርን ለማገልገል በሚያስችል መልኩ ወንድሞችን በማስተባበር መልካም ተፅእኖ የሚፈጥሩበትን ዕድል ማመቻቸት ነው። የዚህ ህብረት መፈጠር ለብዙ ቅን ዜጎች ሃገርና ወገንን ለመርዳት ያላቸውን ህልም እውን ለማድረግ እድሉን ማስገኘቱ ብቻ ሳይሆን ላለፉት ብዙ አመታት በልዩነታችን ላይ በማተኮር ማህበረሰባችን እርስ በእርስ እንዳንረዳዳና እንዳንተጋገዝ የተጫነብንን መርገም ገፎ ሁላችንም ለሁላችን የምንቆምብትን የአንድነት መንፈስ የሚያበስር ታላቅ ድል ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ መሪ አፄ ምኒሊክ ለአድዋ ዘመቻ ጥሪ ሲያደርጉ አመልህን በጉያ ስንቅህን በአህያ ጭነህ ተከተለኝ እንዳሉት እኛም ያሉንን ልዩነቶች ለየራሳችን በመያዝ ለጋራ ዕድገትና ትብብር በህብረት በመነሳት እውነተኛ የሃገር ፍቅርና የወገን ክብር ያለን ወንድሞች ሁሉ ይህንኑ በተግባር ለማስመስከር ያለንን የእውቀት; የጉልበትና የገንዘብ ስንቃችንን በመያዝ ይህን ህብረት በመቀላቀልና በማገዝ ስለ ሃገራችን ልማትና ስለህዝባችን ዕድገት ያለንን ብሩህ ተስፋ ዕውን እንድናደርግ ለሁሉም ወንድሞች ጥሪአችንን እናቀርባለን።
Quotes
![]() ከወንድም ግሩም ለማ (ዶክተር) ሰዎች በጠቅላላው ማህበራዊ ፍጥረት ነን። ደስ ሲለን ከሰው ጋር ሆነን የደስታ ጊዜያችንን ማሳለፍ እንፈልጋለን። ስናዝንም ሰዎች አብረውን ሲሆኑ መፅናናት ይሆንልናል። ስንታመም የሰዎች አብሮ መሆን ያበረታናል። በዘመናት መካከል የአብሮነትን ጠቃሚነት በተለያዩ ምሳሌዎች ተገልጿል። ድር ቢያብር አንበሳ ያስር። ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ለ ሃምሳ ሰው ጌጥ። በሶስት የተገመደ ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም እና ሌሎችም። ባለፈው አንድ አመት ውስጥ በወር አንድ ጊዜ የተለያየ የህይወት ልምድ ካላቸው ወንድሞች ጋር በመነጋገር ያገኘሁት ትምህርትና ልምድ በጣም ብዙ ነው። ይህ ሕብረት ደግሞ የበለጠ አድጎ ራስን በማሳደግ ሌሎችም እንዲያድጉ በመርዳት ለቤተሰባቸው ለአካባቢያቸው እንዲሁም ለሃገራቸው የሚጠቅሙ ዜጎች ያደርጋል የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ። |
![]() ከወንድም ሙሉጌታ አርአያ በመጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ 23 ቁጥር 19 ላይ "ልጄ ሆይ ስማ ጠቢብም ሁን ልብህንም በቀናው መንገድ ምራ" ተብሎ እንደተጻፈው ቅዱስ ቃል ልባችንን ይበልጥ በቀናው መንገድ ለመምራትና ከቅጥራችን ወጣ ብለን ክርስቲያናዊ ግዴታችንን ለመወጣት በማሰብ እነሆ ይህን ኅብረት መሰረትን። ከመራራቅ መቀራረብ ተስፋን ያጎላል እንዲሉ ብሩህ ተስፋም እይታን ያሰፋል፣ እምነትንና ጥንካሬ እንዲኖረን ያግዛል ብለን እናምናለን። ይህ ኅብረት በአካባቢያችን የሚታዩ የጎላ ችግሮችን ለመታደግ መንገድ ከፋች ይሆናል ብለንም እናስባለን። እግዚአብሔር በረዳን መጠንና አቅሙና ጉልበቱ እንደፈቀደ በምድራችን ላይ የኅብረታችንን አሻራ ለመጣል እንደምንችል ተስፋ አለን። በሜኔሶታ የምትገኙ ወገኖች ኅብረታችን ለማንኛውም ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ክፍት መሆኑን እያሳሰብን የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድበን ለወገኖቻችን መልካም ነገር በማድረግ ተስፋቸውን ብሩህ ለማድረግ ከኅብረታችን እንድትቀላቀሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። |
![]()
"#He_is_not_heavy_he_is_my_brother." |